Showing posts with label Ethiopia. Show all posts
Showing posts with label Ethiopia. Show all posts

Wednesday, November 13, 2013

ዳግማዊ ሠለሞን!

መቼም ስለ መርካቶ ያልተወራ ነገር ያለ አይመስለኝም….መርካቶን የማያውቃት ይኖራል ለማለትም አልደፍርም፡፡ ከአፍሪካ በስፋቱ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ትልቁ የገበያ ማህከል፡፡መርካቶ!
ስለ መርካቶ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን በግጥም ‹‹አይ መርካቶ›› ተወዳጁ አብዱ ኪያር በዜማ ‹‹መርካቶ ሰፈሬ›› ና ወዘተ የብዙ የጥበብ ሰዎች እጅ ዳሷታል፡፡
እኔ የምለው መርካቶ ውስጥ ካሉ ቦታዎች አውቶብስ ተራ አካባቢ የሚገኘውን አዲስ ከተማ ት/ቤትን አስተውለውት ያውቃሉ?
የቀድሞ ልዑል መኮንን የአሁኑ አዲስ ከተማ መሠናዶ ት/ቤት የሠፈረበት አካካባቢ አስገራሚ ገፅታ ያለው ቦታ ነው፡፡ ት/ቤቱን ለተመለከተው እንዴት ሰው ሊማርበት ይችላል ብሎ ሊገረም እንደሚችል ጥርጥር የለኝም፡፡ እመኑኝ በድፍን ኢትዮጵያ እንደ አዲስ ከተማ አስገራሚ ት/ቤት አይኖርም፡፡
ቀን በእውቀት የታነፁ የአገር ተረካቢዎችን ለማፍራት የሚታትረው ት/ቤት ማታ ማታ በብዙ እንስቶች ተከቦ ይታያል፡፡
አንዳንዴ ዝም ብዬ ስመለከተው ጠቢቡ ሰለሞንን የሆነ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም በሴት የመታጀባቸው ጉዳይ ነው፡፡
የዘመኑ ሰለሞን አዲስ ከተማ አመሻሽ ላይ ልጅነታቸውን ባልጨረሱ ወጣት ሴቶች ተከቦ ማየቱ የተለመደ ነው፡፡

Saturday, May 25, 2013

የቡርቃ ዝምታ የተሰኘውን መፅሐፍ በነፃ ያነቡት

ጋዜጠኛና ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ 
ከታዋቂውና ዝነኛው ጋዜጠኛና ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ መፅሐፎች ውስጥ የቡርቃ ዝምታ የተሰኘውን መፅሐፍ በነፃ ያነቡት ዘንድ ተጋብዘዋል፡፡

Friday, May 3, 2013

ፋሲካና ዶሮ


የፋሲካ በአል የአበሻ ምድር ላይ በተለየ መልኩ ከሚከበሩ በአላት ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ይህን በአል ለየት የሚያደርገው ለአርባ ቀናት ከስጋና መሰል ምግቦች ተከልክሎ የከረመው የምህበኑ ሰውነት በአንድ ቀን ለሊት ውስጥ ያለ የሌለ አቅሙን አፈርጥሞ ለበቀል ሆዱን የሚያሰፋበት፤የእጆቹን መዳፍ  በቅባት የሚያረሰርስበት በአጠቃላይ ዶሮ በተባለች አዕዋፍ (እንስሳት) ላይ አብዮት የሚፈነዳበት የአብዮት በአል ነው፡፡ ወዳጄ የተሰመረባትን ሐረግ ሌላ ፍቺ እንዳይሰጧት እማጸኖታለው፡፡ ምናልባት በአሉ የድህነት እንጂ የአብዮት አይደለም ብሎ ሊሞግት የሚነሳ ካለ ባይደክም ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም ሙሉ በሙሉ የደህንነት በአል ለመሆኑ በሙሉ ልቤ አማኝ ስለሆንኩ….
ፋሲካችን ክርስቶስ በእለተ አሙስ ተይዞ ለፍርድ ወደ ጲላጦስ አደባባይ በሚወሰድበት ወቅት ለሚወደው ደቀ መዝሙሩ ዶሮ ሳይጮህ ሶስት ጊዜ ትክደኛለህ ብሌ ቀድሞ ተናግሮት እንደነበር ቅዱስ መፅሐፍ ይነግረናል፡፡ ቅዱሱ ሰው፤የቤተ ክርስቲያን የአለት መሰረት ታላቁ አዋርያ ጌታውን አላውቀውም ብሎ ሲክደው የክርስቶስን ቅድሚያ ትንቢት የቅዱስ ጴጥሮስን ክህደት ቆጥራ የመሰከረች ይህች ዶሮ ዛሬ ላይ ክፉኛ ተጨቁና ለፆም መፈሰኪያ መዋሏን ስናይ (በተለይ ለአቢሲኒያውያን) ነገሩ ምን ያህል ትስስር እንዳለው እንረዳለን፡፡ በቅዱስ ጴጥሮስ ፊት አውራሪነት የተመሰረተችው ቤተ ክርስቲያን ምዕመኖቿ ፋሲካቸውን በዶሮ መፈሰካቸው ምናልባትም ለምን አሽቃበትሽ በሚል የበቀል እርምጃ እየተወሰደባት ለመሆኖም ግምት ሰቶ ማለፍ ይቻላል፡፡

Wednesday, April 24, 2013

የኢሰፓ ሊቀመንበር የነበሩት ኮሎኔል መንግስቱ በልብ በሽታ .መሞት.....



menegestu
Mengestu h/mariam with Fidel kastero
የዛሬ የማህበራዊ ድህረ ገፅ ወሬዎች በቀድሞ የኢሰፓ ሊቀመንበር በነበሩት ኮሎኔል መንግስቱ ሃ/ማርያም ሆኗል፡፡ ኮሎኔሉ በልብ በሽታ እነደሞቱ ጥቂት የማይባሉ የማህበራዊ ድህረ ገፅ ታዳሚዎች መርዶውን እየነገሩን ነው፡፡ የኮሎኔሉን መሞት መንግስት ከዘረጋው መልካም አስተዳደር የመነጨ ስለመሆኖም አንዳንዶች እየደሰኮሩ ስንሰማ ባላንጣችንን ሞት ክብር ላንተ እንድል አስገድዶናል፡፡ መንግስቱ ደግም ሰሩ ክፉ የዚህች ድሃ አገር ገዥ ሆነው ለ 17 አመታት ኖረዋል፡፡ በመሞታቸው መደሰት ሳይሆን እንሲቪላይዝድ ሰው ቤተሰባቸውን ባናፅናናም ክፉ መናገሩን በበኩሌ የማልደግፈው ነው፡፡ አትዮጵያ ባትቀድምም አትዮጵያ ትቅደምን እንድናዜም ያረጉ ሶሻሊስት ኢትዮጵያን ለመገንባት ግንባር ድረስ የሄዱ ትጉህ ወታደር ኋላም ጥሩ ፈርጣጭ ነበሩና የእውነት ሞተው እንኳን ቢሆን ነብሳቸውን ይማርልን ብለን ኢትዮጵያዊ ጨዋነታችንን እናሳይ እላለው፡፡

Sunday, April 14, 2013

አበሻ ኩሩ ነው!?

የትኛው አበሻ? የድሮው ወይስ የአሁኑ? እውን በምናችን ይሆን እንዲ አበሻ ኩሩ ነው በሚል ብሂል ውጥርጥር ያልነው፡፡ ቲሸርቶቻችን የሚናገሩት ስለኩሩነታችን፤ስለጀግንነታችንና ስለብዝሃነታችን ከሆነ ሰንበትበት ብሏል፡፡ኩሩ ማህበረሰብ ለራሱ የተለየ ቦታ ያለውና ሌሎች ላይ የማይደርስ በሎሎች የተከበረ ለመሆኑም የማህበረሰብ ሳይንስ ሊቃውንት የሚስማሙበት አቅ ነው፡፡
የአበሻ ኩሩነት እንደቻይናውያን እንቁራሪት አለመብላቱና ምግብ መምረጡ ከሆነ ኩሩነት ትርጉሙ መቀየር አለበት ባይ ነኝ፡፡ ኩሩነታችን አለመንበርከካችንና በነጭ አለመገዛታችን  ነው የምንል ከሆነ ደግሞ ለዚህ ዘመን አበሾች የማይመጥን ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ነጮች እንደዋዛ ክብራችንን ከነጠቁን ዘመናት አለፉ....በቱሪስት መዳረሻ በሆኑ ከተሞቻችን  ኩሩው አበሻ ለፈረንጆች የሚያሳየውን ፍቅር ስንመለከት ሰውኛ የሆነ የጨዋ ሕዝብ ልዩ ምልክት መሆኑን እንታዘብና ወደራሳችን ተመልሰን ጓዳችንን ስናይ የሰውኛ ባህሪ መሆኑ ይጠፋብንና አድር ባይነታችን ይጎላብናል፡፡ ሴቶቻችን የአበሻ ወንድ በአፍንጫዬ ካሉም ሰንበትበት ብለዋል...ቄሶቻችን በቤተ እምነት መዘክር ውስጥ ‹‹ፈረንጅ መቷል ውጡ›› ማለት ከጀመሩም አመታት አለፉ፡፡ ማለፍ ክልክል ነው፤መንገዱ ዝግ ነው በሚባሉ ቦታዎች ላይ አበሾች ተኮልኩለው ነጭ እንደዋዛ ሲያልፍና ፍቃድ ሲሰጠው ስናይ ልማታዊነታችን ታውሶን በቸልታ የምናልፈው የእለት ተእለት ተራ ጉዳይ ከሆነም ሰንብቷል፡፡ ኩሩነት በአባቶች ታሪክ መታበይ ከሆነ እውነት ኩሩ አለመሆናችንን ላስረግጥ እወዳለው፡፡
የአበሻ ኩሩነት በጎዳና የወደቀውን ወንድሙን የሚያንቋሽሽና አለውልህ ከማለት የኘጮችን በጎነት የሚናፍቅ እከሌ እኮ እስፖንሰር አግኝቶ....የምንል የጉድ ልጆች ከንቱ ኩራት... ሲረግጡን የምንረገጥ የራሳችን ማንነት የጠፋብን ተአምር ጠባቂዎች፤የምላስ ቁማርተኞች፤ሆዳችን ክብራችን የሆነ ዘመነኛ ኩሩዎች!
ወዳጄ ኩሩ ነኝ ብለህ ታስባለህ? እንግዲያውስ ለራስህ ቦታ ይኑርህ፤እራስህን አክብር፤ በቆዳ ልዩነት የማታምን ቅድሚያ ለኢትዮጵያዊው ወንድሜ የሚል አትዮጵያዊ ብሔርተኛ ሁን!!
በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ወደፊት በሰፊው እናወጋለን፡፡

Tuesday, April 9, 2013

የሕዝብ ልጅ ምንግዜም የሕዝብ ነው!

Temesgen desalghe
የሕዝብ ልጅ ምንግዜም የሕዝብ ነው!
ግዛው ስለሺ ጃኖ መፅሔት ቅፅ 1 ቁጥር 2 ላይ የሰማኒያ አመቱ አዛውንትና የአምስት አመቱ ፈረሳቸው ብሎ የፃፈውን ፅሁፍ ላነበበ ሰው በእርግጠኝነት ስለፀሐፊው የሚኖረው አመለካከት የተዛባ ነው የሚሆነው፡፡አቶ ግዛው ማመዛን የከበደው ሰው ለመመሆኑም መስካሪ አያሻም፡፡ በግል ፕሬስ ማሊያ የሕዝብ ልጆችን ላማጥላላት ታጥቆ የተነሳ ባንዳ መሆኑን ከፅሁፉ ጭብጥ መረዳት አያዳግትም፡፡
የሰማኒያ አመት አዛውንት የተባሉት ፕሮፌሰር መስፍን በአምስት አመት በተመሰላው ተመስገን ደሳለኝ መፅሔትና ጋዜጣ ላይ የሚያወጡት መጣጥፎች የአንባቢን ቀልብ የሚስቡና ጠማማውን ለማቅናት የሚታትር፤ ገዥውን የሚያስተምር መሆናቸውን የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ በፅኑ ያምናል፡፡ እኚህ ምሁር በስተርጅና ፈርሆንን የሚቃወሙበት ምክንያት የስልጣን ጥማት ስላላቸው ነው ተብሎ የሚታመን እንኳን ቢሆን በፍትህ፤በአዲስ ታይምስ እንዲሁም የእሳት እራት በሆነችው ልህልና መፅሔት ላይ ቋሚ አምደኛ በመሆን የሚያወጧቸው ፅሁፎች የበሰሉ ትችቶችና ፍትህና ዲሞክራሲን ናፋቂዎች ለመሆናቸው ማንም ሊመሰክረው የሚችለው አቅ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ አቶ ግዛው ስለሺ ምንም እንኳን ስለፕሮፌሰሩ የኋላ ታሪክ ቢነግረንም ምሁሩ ላይ ያለውን የመረረ ጥላቻ ያሳብቁበታል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና በመላው አገሪቱ በሚገኙ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ ምሁራን ሊነግሩን ያልደፈሩትንና ከመሞት መሰንበት በሚል አገርኛ ብሂል አድር ባይነትን መርጠው አፋቸውን ለጉመው በተቀመጡበት ወቅታዊ የአገራችን ችግሮች ላይ እንዲሁም የታሪክ አመክንዮ ላይ እኚህ ምሁር የሠላ አስተያየቶችንና የተጣመመ የታሪክ አተያዮችን(ኢትዮጵያ የመቶ አመት ታሪክ ያላት አገር ነች እና የመሳሰሉትን) በማቅናትና እውነትን በመመስከር ለሚያበረክቱት አስተዋፅሆ ምስጋና መቸር ሲገባን የስልጣን ጥማተኛ አስመስሎ ማብጠልጠሉ ነገ ከአድር ባይነት ተላቀው በቀናነት ለመስራት ለሚነሱ ምሁራን ታላቅ እንቅፋት መሆኑ እሙን ነው፡፡

Sunday, February 10, 2013

ሃ/ማርያም ሆይ ጫማው ሰፍቶዎታል!!!

ሃ/ማርያም ሆይ ጫማው ሰፍቶዎታል!!!

የሠዎች አስተሳሰብ በኖሩበት ማህበረሰብ እንዲሁም በግለሰባዊ ማንነት ላይ ተመርኩዞ የተለያየ እንደሚሆን እሙን
ነው፡፡ከአንድ ማህፀን በወጡ ሁለት መንትያ ልጆች መካከል እንኳን የሚኖረው የአስተሳሰብ ልዩነት ስንመለከት ሠዎች
በየትኛውም መለከኪያ ተመሳሳይ የሆነ የአስተሳሰብ ደረጃ ሊኖራቸው እንደማይችል እንረዳለን፡፡ በአንድ ነገር ላይ
ተመሳሳይ አቋም ቢኖረንም ነገሩን የምንረዳበት መንገድና የአፈፃፀሙ ሁኔታ ከሰው ሰው ተለያይቶም እንመለከታለን፡፡
የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ልሂቃን የሆኑት መሪዎቻችን በአንድ ልብ እናስብ በአንድ ቃል እናውራ ብለው መነሳታቸው
ምናልባትም በመንፈሳዊ ሕይወታችን የምናውቃቸው የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ሰልስቱ ምዕት እንደ አንድ ልብ አሳቢ
እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በመሆን በቤተክርስቲያን ላይ ክህደት የፈፀሙትን ሰዎች አውግዘው እንደነበር ድርሳናት
ያወሱትን እንድናስታውስ ይጋብዘናል፡፡ መቼም መለኮታዊ ሃይል ካልዳሰሰን በቀር ሠዎች በአመለካከትና በአነጋገር
ፍፁም አንድ ሆነው ያለአሳብ ልዩነት ነገሮችን ሊወስኑ እንደማይችሉ በቤተሰብ ውስጥ በሚወሰኑ ውሳኔዎች እንኳን
መታዘብ እንችላለን፡፡(ፈላጭ ቆራጭ አባወራ ካልሆነ፡፡)
ላለፉት 20 እና 21 አመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ፓርላማ ውስጥ ነገሮች ሲወሰኑ መለኮታዊ ሃይል የዳሰሳቸው ይመስል
ያለ አንዳች ክርክርና ተቃውሞ ውሳኔዎች ሲወሰኑ አይተናል፡፡መቼም ያለአሳብ ልዩነት ጥሩ ነገር ማግኘት አይቻልም
እንዲሁም የተሻለውን መወሰን ፍፁም ከባድ መሆኑንና ተከትሎት የሚመጣውም ውጤት አስደሳች እንደማይሆን መረዳቱ
አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ አምባ ገነኖች ለሚያነሱት አሳብ ተቃውሞን እንደማይሹ የፓርላማ ውስጥ ሽሙጥና ዘለፋ ምስክር
ነው፡፡በአለም ላይ ስልጣን የያዙ አምባገነን መሪዎች ሁሉ ተመሳሳይ የሚያደርጋቸው ባህሪ ቢኖር ለሕብረተሰቡ
እናውቅልሃለን፤እኛ ከሌለን…የሚሉ ፈሊጦችን በአደባባይ መፎከር ነው፡፡አብዮታዊ መሪዎቻችን ቢሆኑም ለኢትዮጵያውያን
እናውቅልሃለን ከማለት ውጭ ፍላጎታችንን ጠይቀውን አያውቁም፡፡በየቀበሌው የሚደረገው ሕብረተሰባዊ ተሳትፎ
የሚያሰፈልገው ስብሰባም ቢሆን ፖለቲካዊ ፋይዳው እንጂ ለህብረተሰቡ የሚያስገኘው አንዳችም ኢኮኖሚያዊም ይሁን
ማህበራዊ ጥቅም እንደሌለ ኑሮዋችን በቂ ምስክር ነው፡፡
የሆነው ሆኖ መጤው ጠ/ሚንስትር የቀድሞውን ጠ/ሚንስትር ጫማ በማጥለቅ የግል ባህሪያቸውንና ውስጣቸው የተደበቀውን
ሃይል እያጠፉ ያለ ይመስለኛል፡፡ ሠው እንደራሱ እንጂ እንደጎረቤቱ አይኖርም የሚለው ኢትዮጵያዊው ብሂል እዚህ
ጋር ወሃ ቋጥሮ እናገኘዋለን፡፡አቶ ሃ/ማሪያም እንደራሳቸው እንጂ እንደ አቶ መለስ ሊመሩን ከቶውንም አይገባም፡፡
እንደሚታወቀው የአቶ መለስ ጥንካሬ ፓርቲያቸውን ጠንካራ ከማድረግ አልፎ የሚኒሊክን ቤተ መንግስት የግላቸው
እስከማድረግ አድርሷቸዋል፡፡ ደግም ይሁን ክፉ በታጋዩ ፈርሆን የግል አመለካከትና ጥንካሬ አገሪቷ ላይ ለ21
አመት  ያሻቸውን ሲፈፅሙ እንደነበር የወራት ትዝታችን መሆኑን ከሞቱ በኋላ በትግል ጓዶቻቸው
ተመስክሮላቸዋል፡፡አቶ መለስ ከአልባኒያን ስርዓት እስከ ልማታዊ መንግስትነት ያደረሳቸው የራሳቸው የግል
አመለካከትን በለሌች ላይ በተለይ በትግል ጓዶቻቸው ላይ የማሳረፍ ታለቅ ተሰጥሆ ስለነበራቸው ነው፡፡(የአብዮታዊ
ዲሞክራሲ ልሂቃን ትግላቸው የአልባኒያ አይነት ስርዓት በኢትዮጵያ ለማምጣት እንደነበር የምንዘነጋው
አይደለም፡፡የሚገርመው ነገር መገንባት የሚፈልጉት ስርሃት ጨቋኝ በሚባለው መንግስቱ እንኳን የማይደገፍ መሆኑ
ነው፡፡በወቅቱ አልባኒያ በሆጃዎች ትመራ የነበር ፍፁም አምባ ገነንነት የሰፈነባት አገር ነበረች፡፡)