Friday, January 16, 2015

አንድ…ሶስት




አራት በአራት በሆነች ክፍል ውስጥ ረሃ እየሆኑ ነው፡፡ አንዱን ሲጥሉ አንዱን ሲያነሱ ታላቅ የአሳብ ባህር ውስጥ ገብተው ስለሕይወት ይፈላሰፉ ጀምረዋል፡፡ የፊት ገፅታቸው ተቀያይሯል….አይኖቻቸው ልውጣ ልውጣ የሚሉ ይመስላሉ፡፡ ፈጠዋል፡፡ የቤቱ ሙቀት የሲጋራው ጢስ ታክሎበት ፊትን ይጋራፋል፡፡ ሶስት ብቻ በመሆናቸው ተጠባብቆ ለማውራት አመችቷቸዋል፡፡የማህበረሰቡን ወግ መኮነን ተያይዘውታል፤ከግለሰብ ማንነታቸው ጋር ሊሄድ ባልቻለው ማህበረሰብ ውስጥ ተፈጥረው ማድረግ የፈለጉትን የሞራል ሕግ በሚል ጠፍሮ የያዛቸውን የቡድን ሕግ በማውገዝ ላይ ናቸው፡፡ ሞራል ደካሞችና ፈሪዎች ጠንካሮችን የሚያስሩበት ሰንሰለት መሆኑን መተማመን ችለዋል፡፡ The only good man is the man who succeeds የምትለዋ የኒቼ አሳብ አጥንታቸው ድረስ ዘልቆ ተሰምቷቸዋል፡፡ አሸናፊዎች ሁሌም ጉዞ ላይ ናቸው፤በጉዞው የደከሙትና መረሳት ያልፈለጉት የሞራልን ጉዳይ በማንሳት በጉዞዋቸው ርቀው እንዳይሔዱ ያደርጋሉ በዚህም በማህበረሰብ ውስጥ የሚበቅሉ አሸናፊዎች ነገራቸው ሁሉ ከማህበረሰቡ አመለካከት አንጻር እየተለካ ለውግዘትና ለመገለል ያበቃቸዋል፡፡
      ትምህርቷን ከአስራ ሁለተኛ ክፍል አቋርጣ ቤት ብትውልም መፅሐፍትን የማንበብ ክፉኛ መንፈስ ተጠናውቷታል፡፡ ማንንም ተናግሮ ማሳመን የተካነችው ለግላጋዋ ወጣት በሁለት ወንዶች መሃል ወሲብን ማውራት የቀለለ ተራ ነገር አድርጋዋለች፡፡ የሁለቱን ወጣቶች ጆሮ ለጉድ ተቆጣጥራዋለች፡፡ ታወራለች፤ይሰሟታል፡፡