የፋሲካ በአል የአበሻ ምድር ላይ በተለየ መልኩ ከሚከበሩ በአላት ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ይህን በአል ለየት የሚያደርገው ለአርባ ቀናት ከስጋና መሰል ምግቦች ተከልክሎ የከረመው የምህበኑ ሰውነት በአንድ ቀን ለሊት ውስጥ ያለ የሌለ አቅሙን አፈርጥሞ ለበቀል ሆዱን የሚያሰፋበት፤የእጆቹን መዳፍ በቅባት የሚያረሰርስበት በአጠቃላይ ዶሮ በተባለች አዕዋፍ (እንስሳት) ላይ አብዮት የሚፈነዳበት የአብዮት በአል ነው፡፡ ወዳጄ የተሰመረባትን ሐረግ ሌላ ፍቺ እንዳይሰጧት እማጸኖታለው፡፡ ምናልባት በአሉ የድህነት እንጂ የአብዮት አይደለም ብሎ ሊሞግት የሚነሳ ካለ ባይደክም ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም ሙሉ በሙሉ የደህንነት በአል ለመሆኑ በሙሉ ልቤ አማኝ ስለሆንኩ….
ፋሲካችን ክርስቶስ በእለተ አሙስ ተይዞ ለፍርድ ወደ ጲላጦስ አደባባይ በሚወሰድበት ወቅት ለሚወደው ደቀ መዝሙሩ ዶሮ ሳይጮህ ሶስት ጊዜ ትክደኛለህ ብሌ ቀድሞ ተናግሮት እንደነበር ቅዱስ መፅሐፍ ይነግረናል፡፡ ቅዱሱ ሰው፤የቤተ ክርስቲያን የአለት መሰረት ታላቁ አዋርያ ጌታውን አላውቀውም ብሎ ሲክደው የክርስቶስን ቅድሚያ ትንቢት የቅዱስ ጴጥሮስን ክህደት ቆጥራ የመሰከረች ይህች ዶሮ ዛሬ ላይ ክፉኛ ተጨቁና ለፆም መፈሰኪያ መዋሏን ስናይ (በተለይ ለአቢሲኒያውያን) ነገሩ ምን ያህል ትስስር እንዳለው እንረዳለን፡፡ በቅዱስ ጴጥሮስ ፊት አውራሪነት የተመሰረተችው ቤተ ክርስቲያን ምዕመኖቿ ፋሲካቸውን በዶሮ መፈሰካቸው ምናልባትም ለምን አሽቃበትሽ በሚል የበቀል እርምጃ እየተወሰደባት ለመሆኖም ግምት ሰቶ ማለፍ ይቻላል፡፡