Temesgen desalghe |
ግዛው ስለሺ ጃኖ መፅሔት ቅፅ 1 ቁጥር 2 ላይ የሰማኒያ አመቱ አዛውንትና የአምስት አመቱ ፈረሳቸው ብሎ የፃፈውን ፅሁፍ ላነበበ ሰው በእርግጠኝነት ስለፀሐፊው የሚኖረው አመለካከት የተዛባ ነው የሚሆነው፡፡አቶ ግዛው ማመዛን የከበደው ሰው ለመመሆኑም መስካሪ አያሻም፡፡ በግል ፕሬስ ማሊያ የሕዝብ ልጆችን ላማጥላላት ታጥቆ የተነሳ ባንዳ መሆኑን ከፅሁፉ ጭብጥ መረዳት አያዳግትም፡፡
የሰማኒያ አመት አዛውንት የተባሉት ፕሮፌሰር መስፍን በአምስት አመት በተመሰላው ተመስገን ደሳለኝ መፅሔትና ጋዜጣ ላይ የሚያወጡት መጣጥፎች የአንባቢን ቀልብ የሚስቡና ጠማማውን ለማቅናት የሚታትር፤ ገዥውን የሚያስተምር መሆናቸውን የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ በፅኑ ያምናል፡፡ እኚህ ምሁር በስተርጅና ፈርሆንን የሚቃወሙበት ምክንያት የስልጣን ጥማት ስላላቸው ነው ተብሎ የሚታመን እንኳን ቢሆን በፍትህ፤በአዲስ ታይምስ እንዲሁም የእሳት እራት በሆነችው ልህልና መፅሔት ላይ ቋሚ አምደኛ በመሆን የሚያወጧቸው ፅሁፎች የበሰሉ ትችቶችና ፍትህና ዲሞክራሲን ናፋቂዎች ለመሆናቸው ማንም ሊመሰክረው የሚችለው አቅ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ አቶ ግዛው ስለሺ ምንም እንኳን ስለፕሮፌሰሩ የኋላ ታሪክ ቢነግረንም ምሁሩ ላይ ያለውን የመረረ ጥላቻ ያሳብቁበታል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና በመላው አገሪቱ በሚገኙ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ ምሁራን ሊነግሩን ያልደፈሩትንና ከመሞት መሰንበት በሚል አገርኛ ብሂል አድር ባይነትን መርጠው አፋቸውን ለጉመው በተቀመጡበት ወቅታዊ የአገራችን ችግሮች ላይ እንዲሁም የታሪክ አመክንዮ ላይ እኚህ ምሁር የሠላ አስተያየቶችንና የተጣመመ የታሪክ አተያዮችን(ኢትዮጵያ የመቶ አመት ታሪክ ያላት አገር ነች እና የመሳሰሉትን) በማቅናትና እውነትን በመመስከር ለሚያበረክቱት አስተዋፅሆ ምስጋና መቸር ሲገባን የስልጣን ጥማተኛ አስመስሎ ማብጠልጠሉ ነገ ከአድር ባይነት ተላቀው በቀናነት ለመስራት ለሚነሱ ምሁራን ታላቅ እንቅፋት መሆኑ እሙን ነው፡፡