Sunday, February 10, 2013

ሃ/ማርያም ሆይ ጫማው ሰፍቶዎታል!!!

ሃ/ማርያም ሆይ ጫማው ሰፍቶዎታል!!!

የሠዎች አስተሳሰብ በኖሩበት ማህበረሰብ እንዲሁም በግለሰባዊ ማንነት ላይ ተመርኩዞ የተለያየ እንደሚሆን እሙን
ነው፡፡ከአንድ ማህፀን በወጡ ሁለት መንትያ ልጆች መካከል እንኳን የሚኖረው የአስተሳሰብ ልዩነት ስንመለከት ሠዎች
በየትኛውም መለከኪያ ተመሳሳይ የሆነ የአስተሳሰብ ደረጃ ሊኖራቸው እንደማይችል እንረዳለን፡፡ በአንድ ነገር ላይ
ተመሳሳይ አቋም ቢኖረንም ነገሩን የምንረዳበት መንገድና የአፈፃፀሙ ሁኔታ ከሰው ሰው ተለያይቶም እንመለከታለን፡፡
የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ልሂቃን የሆኑት መሪዎቻችን በአንድ ልብ እናስብ በአንድ ቃል እናውራ ብለው መነሳታቸው
ምናልባትም በመንፈሳዊ ሕይወታችን የምናውቃቸው የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ሰልስቱ ምዕት እንደ አንድ ልብ አሳቢ
እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በመሆን በቤተክርስቲያን ላይ ክህደት የፈፀሙትን ሰዎች አውግዘው እንደነበር ድርሳናት
ያወሱትን እንድናስታውስ ይጋብዘናል፡፡ መቼም መለኮታዊ ሃይል ካልዳሰሰን በቀር ሠዎች በአመለካከትና በአነጋገር
ፍፁም አንድ ሆነው ያለአሳብ ልዩነት ነገሮችን ሊወስኑ እንደማይችሉ በቤተሰብ ውስጥ በሚወሰኑ ውሳኔዎች እንኳን
መታዘብ እንችላለን፡፡(ፈላጭ ቆራጭ አባወራ ካልሆነ፡፡)
ላለፉት 20 እና 21 አመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ፓርላማ ውስጥ ነገሮች ሲወሰኑ መለኮታዊ ሃይል የዳሰሳቸው ይመስል
ያለ አንዳች ክርክርና ተቃውሞ ውሳኔዎች ሲወሰኑ አይተናል፡፡መቼም ያለአሳብ ልዩነት ጥሩ ነገር ማግኘት አይቻልም
እንዲሁም የተሻለውን መወሰን ፍፁም ከባድ መሆኑንና ተከትሎት የሚመጣውም ውጤት አስደሳች እንደማይሆን መረዳቱ
አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ አምባ ገነኖች ለሚያነሱት አሳብ ተቃውሞን እንደማይሹ የፓርላማ ውስጥ ሽሙጥና ዘለፋ ምስክር
ነው፡፡በአለም ላይ ስልጣን የያዙ አምባገነን መሪዎች ሁሉ ተመሳሳይ የሚያደርጋቸው ባህሪ ቢኖር ለሕብረተሰቡ
እናውቅልሃለን፤እኛ ከሌለን…የሚሉ ፈሊጦችን በአደባባይ መፎከር ነው፡፡አብዮታዊ መሪዎቻችን ቢሆኑም ለኢትዮጵያውያን
እናውቅልሃለን ከማለት ውጭ ፍላጎታችንን ጠይቀውን አያውቁም፡፡በየቀበሌው የሚደረገው ሕብረተሰባዊ ተሳትፎ
የሚያሰፈልገው ስብሰባም ቢሆን ፖለቲካዊ ፋይዳው እንጂ ለህብረተሰቡ የሚያስገኘው አንዳችም ኢኮኖሚያዊም ይሁን
ማህበራዊ ጥቅም እንደሌለ ኑሮዋችን በቂ ምስክር ነው፡፡
የሆነው ሆኖ መጤው ጠ/ሚንስትር የቀድሞውን ጠ/ሚንስትር ጫማ በማጥለቅ የግል ባህሪያቸውንና ውስጣቸው የተደበቀውን
ሃይል እያጠፉ ያለ ይመስለኛል፡፡ ሠው እንደራሱ እንጂ እንደጎረቤቱ አይኖርም የሚለው ኢትዮጵያዊው ብሂል እዚህ
ጋር ወሃ ቋጥሮ እናገኘዋለን፡፡አቶ ሃ/ማሪያም እንደራሳቸው እንጂ እንደ አቶ መለስ ሊመሩን ከቶውንም አይገባም፡፡
እንደሚታወቀው የአቶ መለስ ጥንካሬ ፓርቲያቸውን ጠንካራ ከማድረግ አልፎ የሚኒሊክን ቤተ መንግስት የግላቸው
እስከማድረግ አድርሷቸዋል፡፡ ደግም ይሁን ክፉ በታጋዩ ፈርሆን የግል አመለካከትና ጥንካሬ አገሪቷ ላይ ለ21
አመት  ያሻቸውን ሲፈፅሙ እንደነበር የወራት ትዝታችን መሆኑን ከሞቱ በኋላ በትግል ጓዶቻቸው
ተመስክሮላቸዋል፡፡አቶ መለስ ከአልባኒያን ስርዓት እስከ ልማታዊ መንግስትነት ያደረሳቸው የራሳቸው የግል
አመለካከትን በለሌች ላይ በተለይ በትግል ጓዶቻቸው ላይ የማሳረፍ ታለቅ ተሰጥሆ ስለነበራቸው ነው፡፡(የአብዮታዊ
ዲሞክራሲ ልሂቃን ትግላቸው የአልባኒያ አይነት ስርዓት በኢትዮጵያ ለማምጣት እንደነበር የምንዘነጋው
አይደለም፡፡የሚገርመው ነገር መገንባት የሚፈልጉት ስርሃት ጨቋኝ በሚባለው መንግስቱ እንኳን የማይደገፍ መሆኑ
ነው፡፡በወቅቱ አልባኒያ በሆጃዎች ትመራ የነበር ፍፁም አምባ ገነንነት የሰፈነባት አገር ነበረች፡፡)
በአገሪቱ
ይወጡ የነበሩት ፖሊሲዎችና ሕጎች የመለስ አሻራ አርፎባቸው የፓርቲው አንደበት ይሆናል፡፡የአብዮታዊ ዲሞክራሲም
ብቸኛው ፈጣሪም መለስ ለመሆናቸው ክርክር የሚያሻው ጉዳይ ባይሆንም ይህ የግል ጥረታቸው የሙሉ ፓርቲያቸውን
ይሉኝታ በማግኘት ላለፉት 21 አመት ስንመራበትና እየተመራንበትም እንገኛለን፡፡ እርግጥ ነው ሰውየው እጅግ ብዙ
ታማኝ ሎሌዎቹ ለዚህ ተግባሩ መሳሪያ ይሆኑ ይሆናል የሰውየው የግል አመለካከቱ ትልቁን ቦታ ሊወስድ ይገባል፡፡
ኢህአዴግ በአንድ ግለሰብ የማይመራ፤የአንድ ግለሰብ የበላይነት የለበትም የሚሉ ቧልተኞች ካሉ በአቶ መለስ ሞት
ወቅት የነበረውን የኢቴቪ ዘገባ ደጋግመው እንዲመለከቱ እጋብዛለው፡፡
በመግቢያዬ ለመግለፅ እንደሞከርኩት አስተሳሰባችን ከኖርንበት ማህበረሰብና ከግል ባህሪ ጋር ተያይዞ ለውጥ ማሳየቱ
የግድ ነው፡፡አቶ መለስ ረጅም የሚባለውን ዘመናቸውን በበረሃ የጥይት ባሩድ በማሽተት ያሳለፉ ታጋይ ሲሆኑ ስልጣን
ለሳቸው የትግል ውጤት የማይቀለበስ የደም ዋጋ ያለው ዘላለማዊ ክብር ነው፡፡በተቃራኒው የአቶ ሃ/ማሪያም
የኑሮዘይቤ ከአቶ መለስ የተለየና የእድሜያቸው እኩሌታ በትምህርት አለም ያሳለፉ አንጋፋ የውሃ ምህንድስና ባለሙያ
ናቸው፡፡ ስለዚህም ስልጣን ለአቶ ሃ/ማሪያም የደም ዋጋ እያስባለ የሚያስፎክር ዘላለማዊ ፀጋ ሳይሆን የህዝብ
አገልጋይነትን መንፈስ የተላበሰ፤ለሕግ የተገዛ፤በሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የሚያምን፤ተቃዋሚዎችን እንደ ፀረ ሰላም
ሳይሆን ጥንካሬው አድርጎ የሚወስድ፤ብዕርተኞችን አሸባሪ ሳይሆን ስህተትን ነጋሪ አጋር አድርጎ የሚወስድ ይሆናል
የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ ነገር ግን ይህን ግምቴ ስህተት የሚያደርገው ብዙ ግድፈቶች እንዳሉ ግን የአደባባይ
ምስጢር ነው፡፡ በአንድ ወቅት ኮረኔል መንግስቱ ዶ/ር ሪካርዶ ኦሪዚዮ ለተባለ ጣሊያናዊ ጋዜጠኛ ‹‹ኢትዮጵያ
ውስጥ አንድ አባባል አለን፡፡ዓለም አዲስ ጫማ ካልተጫማቹ እያለ ይወተውተናል፡፡ከእኛ የሚጠበቀው ደግሞ እግራችንን
ለዚህ ለአዲሱ ጫማ እንዲስማማ ማድረግ ነው፡፡ይሁንና አንዳንድ ጊዜ አዲስ ጫማ የሰዎችን እግር ክፉኛ ስለሚልጣቸው
 አውልቀው ይጥሉታል፡፡ለመሆኑ ይህን እርስ በርሱ የሚቃረን የሚመስል አባባል ተረድተኸዋል? እናንተ ምዕራባውያን
የምትሰሩልንን ጫማ ለእግራችን እንዲስማማ አድርጋቹ በማዘጋጀት ፈንታ የምትጠይቁን በተቃራኒው ነው፡፡ ብቻ ምንም
ተባለ ፤ምንም ተሰራ፤እኔ የሰጠሁት ነጠላ ጫማ እስካሁን ድረስ አልተጣለም፡፡›› ይህ ንግግራቸው ለአብዮታውያኑ
የፖለቲካ ስራ ሁነኛ አባባል ነው፡፡ ደርግ አባላቱን እንደአሸን በማፍላት ለ17 አመታት ለብቻው በማን አለብኝነት
ተቃዋሚዎችን ሲያሳድድና ሲገድል ኖሯል፡፡የደርግን ነጠላ ጫማ የተጫሙት ታጋይ መለስም ተቃውሞ የሚባል መስማት
የማይፈልጉ ታግለን ይዘናል ታግላቹ ያዙ በሚል ፈሊጥ በብቸኝነት ላለፉት 21 አመታት ኢትዮጵያን
ሲመሯት፤አባላቶቻቸውንም እንደአሸን ሲያፈሉ ቆይተው አይቀሬው ይዟቸው ሄደ፡፡ አሁን ደግሞ አቶ ሃ/ማርያም
የመለስን ጫማ በመጫማት ለአዲስ ነገር ጀርባቸውን በመስጠት ራዕይ አስፈፃሚ ለመሆን ራሳቸው ላይ ፈርደዋል፡፡
በየሄዱበት መድረክ ስለመለስ ክብር እንጂ ስለኢትዮጵያ መፃሂ እድል ቁባቸው አይደለም፡፡ የመለስ ራዕይ፤የመለስ
ጅምሮች፤የትራንስፎርሜሽኑ መሃንዲስ….ወዘተ ዝባዝንኬ ላፓርቲያቸው እርችት እንዲሁም በሰሩትም ባልሰሩትም
መመስገንና መመለክ አለባቸው ለሚባለው ለመለስ ሌጋሲ እንጂ ለሃ/ማርያም ምንም ፋይዳ አለመኖሩን ነጋሪ
አያሻውም፡፡አንድ ሰው ለሰራው ስራ ክብር መስጠት ተቀባይነት ያለው ቢሆንም የጠፉትን ጥፋቶች እንዳልተከሰቱ
እስኪመስሉ ማብዛቱ እራስን ለታሪክ ፍርደኛ አሳልፎ መስጠት ነው፡፡(መቼም በዚሁ ከቀጠለ የሐይቲ መሪ እንደነበሩት
ፓፓ ዶክ ምስላቸውን በአይማኖታዊ ቤተመቅደሶቻችን አንጠልጥሉ ሳንባል አንቀርም፡፡)
አቶ ሃ/ማርያም እንደራሱ ሊመራን እንጂ እንዳለፉት አንባገነን መሪ ሊመራን እንደማይገባ እምነቴ ነው፡፡አቶ
ሃ/ማርያም ውስጣቸው የተደበቀውን ሃይል ሊያወጡትና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ ሊሰሩ፤ ካለንበት የድህነት አረንቋና
የዲሞክራሲ ጥማት ሊያላቅቁን እድል ፊቷን መልሳለች፡፡የፓርላማ ውስጥ ክርክር፤የጋዜጠኞች ነፃነት፤የዲሞክራሲ
መርሆች ከቃል ጌጥነት አልፈው በተግባር መሬት ላይ ልናያቸው ተስፈኞች ነን፡፡ ለግዜያዊ ፖለቲካዊ ትርፍና የራስን
የስልጣን እድሜ ከማራዘም ተቆጥበው ጥልቅ በሆነ የአገር ፍቅር ስሜት ሕዝብሆን የድህነትን ባህር እንደሚያሻግሩም
አምንቦታለው፡፡ይህን ባያደርጉና በሰው ጫማ የስልጣን ዘመንዎ ቢያበቃ በታሪክ ትልቁ ተወቃሽ እንደሚሆኑ
አይዘንጉ፡፡ ስለዚህም ክቡር አቶ ሃ/ማርያም ሆይ እራስዎን ይሁኑ፤የራስዎን ጫማ በልክዎ እራስዎ ይስሩ ታላቁ
ክብርዎንም ለማንም አሳልፈው አይስጡ እልዎታለው፡፡
ቸር ይግጠመን!

No comments:

Post a Comment