Tuesday, April 9, 2013

የሕዝብ ልጅ ምንግዜም የሕዝብ ነው!

Temesgen desalghe
የሕዝብ ልጅ ምንግዜም የሕዝብ ነው!
ግዛው ስለሺ ጃኖ መፅሔት ቅፅ 1 ቁጥር 2 ላይ የሰማኒያ አመቱ አዛውንትና የአምስት አመቱ ፈረሳቸው ብሎ የፃፈውን ፅሁፍ ላነበበ ሰው በእርግጠኝነት ስለፀሐፊው የሚኖረው አመለካከት የተዛባ ነው የሚሆነው፡፡አቶ ግዛው ማመዛን የከበደው ሰው ለመመሆኑም መስካሪ አያሻም፡፡ በግል ፕሬስ ማሊያ የሕዝብ ልጆችን ላማጥላላት ታጥቆ የተነሳ ባንዳ መሆኑን ከፅሁፉ ጭብጥ መረዳት አያዳግትም፡፡
የሰማኒያ አመት አዛውንት የተባሉት ፕሮፌሰር መስፍን በአምስት አመት በተመሰላው ተመስገን ደሳለኝ መፅሔትና ጋዜጣ ላይ የሚያወጡት መጣጥፎች የአንባቢን ቀልብ የሚስቡና ጠማማውን ለማቅናት የሚታትር፤ ገዥውን የሚያስተምር መሆናቸውን የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ በፅኑ ያምናል፡፡ እኚህ ምሁር በስተርጅና ፈርሆንን የሚቃወሙበት ምክንያት የስልጣን ጥማት ስላላቸው ነው ተብሎ የሚታመን እንኳን ቢሆን በፍትህ፤በአዲስ ታይምስ እንዲሁም የእሳት እራት በሆነችው ልህልና መፅሔት ላይ ቋሚ አምደኛ በመሆን የሚያወጧቸው ፅሁፎች የበሰሉ ትችቶችና ፍትህና ዲሞክራሲን ናፋቂዎች ለመሆናቸው ማንም ሊመሰክረው የሚችለው አቅ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ አቶ ግዛው ስለሺ ምንም እንኳን ስለፕሮፌሰሩ የኋላ ታሪክ ቢነግረንም ምሁሩ ላይ ያለውን የመረረ ጥላቻ ያሳብቁበታል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና በመላው አገሪቱ በሚገኙ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ ምሁራን ሊነግሩን ያልደፈሩትንና ከመሞት መሰንበት በሚል አገርኛ ብሂል አድር ባይነትን መርጠው አፋቸውን ለጉመው በተቀመጡበት ወቅታዊ የአገራችን ችግሮች ላይ እንዲሁም የታሪክ አመክንዮ ላይ እኚህ ምሁር የሠላ አስተያየቶችንና የተጣመመ የታሪክ አተያዮችን(ኢትዮጵያ የመቶ አመት ታሪክ ያላት አገር ነች እና የመሳሰሉትን) በማቅናትና እውነትን በመመስከር ለሚያበረክቱት አስተዋፅሆ ምስጋና መቸር ሲገባን የስልጣን ጥማተኛ አስመስሎ ማብጠልጠሉ ነገ ከአድር ባይነት ተላቀው በቀናነት ለመስራት ለሚነሱ ምሁራን ታላቅ እንቅፋት መሆኑ እሙን ነው፡፡

ሌላው የአቶ ግዛው የተመረዘ ብህር ያረፈው ወጣቱና አንጋፋው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ ነው፡፡ መቼም አንድ አመዛዝናለው ከሚል ሰው ሊያውም ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን  ደፍሮ የማብጠልጠል አቅም ይኖረዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይህ ወጣት ለብዙዎቻችን ምሳሌ የሚሆን ታላቅ ብዕርተኛ ነው፡፡ስለመንግስት በግልፅ ልናውቃቸው ያልቻልናቸውን የተደበቁ ምስጢሮች ፈልፍሎ በማውጣት፤ወጣቱም የፍትህና የዲሞክራሲ ጥማቱን መቁረጥ የሚችልበትን መንገድ ከታሪክና ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር በማቀናጀት ተስፋችን እጃችን ላይ መሆኑን ደጋግሞ የሚነግረን የኢትዮጵያ ትንሳኤ አብሳሪ ውድ ልጃችን ነው፡፡ ተመስገን እንደሙያ አጋሮቹ ወደ አሜሪካና አውሮፓ አገራት በማምራት የግል ሕይወቱን ማበጀት አሊያም ቤቱን ዘግቶ መቀመጥና የፋሽን መፅሔት (ሁሉም የፋሽን መፅሔት ለማለት አይደለም) በማዘጋጀት ወጣቱን ራዕይ አልባ ማድረግ አቅቶት አይደለም ከእሳት ጋር ጨዋታ የጀመረው ይልቁንም ድሃውንና ፍትህ ናፋቂ የሆነውን የኢትዮጵያን ሕዝብ በቆራጥነት ለማገልገል በሚል መነሳቱን ከአሳዳጆቹ ሁኔታ እንኳን መረዳት አያዳግትም፡፡
ይህን የሕዝብ ልጅ ተላላኪ በማስመሰልና የሰዎች መጠቀሚያ እየሆነ እንደሆነ በመሳል አቶ ግዛው ሊጠቀም የሚችለው ነገር ምን ሊሆን እንደሚችል ፈፅሞ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ምናልባትም የፈርሆን እጆች እርዝመታቸው የግሉንም ፕሬስ ሳይዳስሰው እንዳልቀረ ጥርጣሬው ጎልቶብኛል፡፡ በግሉ ፕሬስ በመጠቀም የግሉን ፕሬስ ትጉሃን በተለመደ የማጥላላት ዘመቻው ከሕዝብ ላማቃረን እየሰራ ለመሆኑም ተቋሚ ሳይሆን አይቀርም የሚል ግምት አድሮብኛል፡፡
ቸር ይግጠመን!

No comments:

Post a Comment