Friday, January 9, 2015

ባህረ ሃሳብ

                   
አየሩ ለዐይን ይይዛል….በብርሃን ነፀብራቅ ውበታቸው የሚገዛን የቀኑ ሙሽሮች ጠቆርቆር ብለዋል፡፡ ለወትሮው በሚያማምር የብረት ዘንግ ተከበው በንፋሱ ግፊት ጣፋጭ በሆነው ለስላሳ ሙዚቃ የሚወዛወዙ አዲስ ሙሽሮች የሚመስሉት ዛፎች ውበታቸው ደብዝዞ ፀጥታ ውጧቸዋል፡፡በአርምሞ ላይ ይመስላሉ፡፡ በዚህ የፀጥታ ወጀብ በፀጥታ መንጎዱ አስፈራኝ፡፡ ይልቅ ከእጅ ስልኬ ላይ ዘፈን ከፍቼ መመሰጡን ምርጫዬ አደረኩት፡፡
     የኔ ፍቅር….ለካ እንዲህ እወድሻለው
     አብረን ሆነን መች አስቤው አውቃለው…….
ሙዚቃው ነው፡፡ እንደወትሮው የሙዚቃው መሳሪያ ቀድሞ ዘፋኙ ይከተላል ስል ዘፋኙ ቀድሞ መሪ ሆኖ አረፈው፡፡ የልጅ የመሰለ ቀጭን ድምፅ ሞቅ ብሎ ጆሮ ላይ ሲስረቀረቅ እንደ ጅብ ጥላ ከብዶ ሰብሰብ ብሎ የነበረው ደመና በሞቅታው ሲበታተን…የሞቀው አየር በአፍንጫዬ ቁልቁል ይተም ጀመር፡፡ ሞቅ አለኝ፡፡ ዙሪያዬን ከበው የሚያዜሙልኝ መላህክትን ያየው ያህል ደስ አለኝ፡፡
     ዳገቱን ጨርሼ አውራ ጎዳናውን ተቀላቀልኩት፡፡ ዘፋኙ መዝፈኑን ቀጥሏል፡፡
          እንዲህ ይጨንቃል ሆይ አንቺን መሸኘቴ
          ባዶ አረግሽኝ የእኔ አመቤቴ
          ሳይታሰብ በድንገት
ልክ ልኬን እየነገረኝ መሰለኝ….ደነገጥኩኝ…ከሳምንት በፊት ዘግቼው የነበረው አጀንዳ በእሊና የፍትህ ጓዳ ተቀሰቀሰ፡፡ ማን ይግባኝ ጠየቀ? ታሳሳኝ የነበረችው የጠዋቷ ፀሐይ የልቤን ንግስት ላላስጨንቃት ለራሴ ቃል ገብቼ ነበር፡፡
     አደቤን ገዝቼ በተቀመጥኩበት በአንዱ ብሩህ ቀን ልብና ዐህምሮዬ አሰጥአገባ ገጥመው ፍቅሬን ይፈትሹ ጀመር፡፡ የልቤን ንግስት አፈቅራታለውን? ምላሹን ከሌላ ሰው አልጠበኩም፡፡ልቤ ይነግረኝ ጀመር….ታፈቅራታለህ! ባታፈቅራት ዕለት ዕለት በማለዳ የምትልክላት የፅሁፍ መልህክት፣አሰልቺው ከሰኃት ደርሶ ሲመጣ ድብርቷን ለማጥፋት ስልኳ ላይ ስትጮህ፤ጩኸትህ አልነሳ ሲል ምን ሆና ይሆን ብለህ ነርቨህን የስራ ጫና ስታበዛበት፣ደግሞም ጨለማው በብርሃን ድልን ሲቀዳጅ ውሎኋን ለመስማት የቆሙት ጆሮዎችህ አሁንም ስልኳ ላይ አጓራ አጓራ ቢልህ…..ዳግመኛ ስሜትህን ሰምተህ ጩኸትህን ብታቀልጠው ማን በጀ ብሎህ? አሁንም ጩኸትህ አይነሳም፡፡ ይሄኔ የከፋውና የፀደቀው መልካሙ አንተነትህ አህምሮህን እረፍት ሲነሱት ከክፋት ደግነት ብለህ ተኝታ ነው….መንገድ ላይ ሆና ነው…ደሞም ከእናቷ ጋር ናት…ብላ ብላ ብላ፡፡ የፀደቀውን አስበህ ፈገግ ስትል ደግማ አለመጮኋ ያበሳጭሃል፡፡ አሁንም ትግል፡፡ የፀደቀው ሙግት ይገጥማል፡፡ ካርድ ጨርሳ ነው…አለበለዚያም የስልኳ ሶፍትዌር ሚስድ ኮል አያሳይ ይሆናል…ብቻ የፍቅርህ ልክ እዚህ ድረስ ነው፡፡ በፍፁም የከፋውን ለማሰብ አትሻም፡፡ ድብን አድርገህ ታፈቅራታለህ!!
     ኦኦ…ልቤ ምቱን ጨመረ..በጠያቂውና ተጠራጣሪው አዕምሮዬ ላይ ድልን መቀዳጀቱ ይበልጥ ስሜታዊ አደረገው፡፡ ነቅዬ ልውጣ ይል ይመስል የደረት ግድግዳዬን ይደበድብ፤መላ ሰውነቴም ሽብር ያርደው ጀመር፡፡ የማጣት ስሜት፣የመለየት ክፉ ጣር ስሜቴን ይንጠኝ ያዘ….ስልክ አለማንሳቷ፣ያለመደወሏ፣ለእነዛ ጣፋጭ የስልክ የፅሁፍ መልዕክቶች ምላሽ አለማግኘቴ አትወደኝ ይሆን በሚል ያንዘፈዝፈኝ ጀመር፡፡
     የሰውነቴ ምቾት ማጣት ለልቤም ሳያሳስበው አልቀረም…የፍቅርን አያልነት ከስሜታዊነት አጉልቶና አርቆ እያሳየኝ ከንቱ ጭንቀቴ ላይ ውሃ ቸለሰበት፡፡ ትወድሃለች! ፍፁም የማጣት ስሜት አይሰማህ….ስለምንስ እይታህ ይጠባል…..ሕይወት ክብ ናት….ምንም ነገር ፈልገህ አታጣም….ሁሉም በጊዜው ውብ ሆኖ ያልፋል፡፡ እስኪ አስበው ህልሟን ያጋራችህ፣ቁርበት ከንፈርህ ከንፈሯ ሲነካው በፀደይ እንደሚፈነዳው ለጋ ፅጌሬዳ ሲፈካ፣አጥንቶችህ የአየር ያህል ቀለውክ ከፍ ብለህ ስትበር….በዚህ ሁሉ ጥልቅ ስሜት ውስጥ ብቻህን አልነበርክም፡፡ ጥልቁ ስሜትህን የተጋራችህ ንግስቴ ብለህ የሾምካት እንስትህ ነች፡፡ እመነኝ የንዳንተ የወደደችው የለም፡፡
     ደሜ ቀዝቀዝ ሲል ይሰማኛል….ቀዝቃዛውን አየር ወደሳንባዬ በሃይል ስቤ አስገባውት፤የስገባውትን አየር አቀጣጥዬ ስተፋው ተነፍቶ እንደተነፈሰ ፊኛ ሙሽሽ አልኩኝ፡፡ እርግጥ ትወደኛለች?...ስፈልጋት ስለምን እራሷን ታርቃለች? ድምጧን ለናፈቀ ጆሮዬ ማላሿ ስለምን ይዘገያል….እንደኔ አይሰማት ይሆን?
ስለምን ልቤን ማመን እንደተሳነው አላውቅም፡፡ ከወራጅ ውሃ ላይ ሳንቲም እንደሚፈነውል ቆርቆሬያለው ምንም በሌለበት አዕምሮዬ ጥያቄዎችን ይፈነቅል ተያይዞታል፡፡
እስኪ አስተውል….ሁሉም ሰላም እኮ ነው!...በሠላሙ እንዲህ መሆንህ ቂልነትህን ገሃድ ያወጣብሃል፤ቁም ነገሩ የእሷ ላንተ ያላት ፍቅር ሳይሆን አንተ ለእሷ ያለህ ፍቅር ብቻ ነው፡፡ ከወደድካት በዝምታ ውደዳት፡፡ ምላሹን የምትጠብቅ ከሆነ ፍቅር መሆኑ ቀርቶ ሞል ውስጥ የሚደረግ ግብይት ይሆናል…ማን ነበር ከፍቅር የሚበልጠው ፍቅር ምላሽ ሳያገኙ ማፍቀር ነው ያለው? እኔንጃ….ምንአልባት ሰይጣን ይሆን? በዘለአለማዊ ቅጣት ከአምላኩ ቢለይም ለአምላኩ ያለውን ፍቅር የአምላክ የሆኑትን በመፈተን ለአምላካቸው ያላቸውን እምነትና ፍቅር ያጠነክራል፡፡ ለአምላኩ ያለው ፍቅር ቅንሃትንም የወለደ ነው…አልታዘዝ ብለው አምላካቸውን የገፉትን ደህና አድርጎ መቅጣትም ያውቅበታል…ዳግመኛ ወደአምላክ ቤት እንዳይገባ በዘለአለማዊ ቅጣት ቢነጥልም ለፈጠረው ያለው ፍቅር ግን አሁንም ዝም ያለ ነው…መልስ የሌለበት፣መልስ የማይጠብቅበት  ፍፁም ፍቅር፡፡
     በስመ አብ ምኑን የማስበው? ለንግስቴ ያለኝ ፍቅር ለእኔ ሳይሆን ለእሷ ስል ሊሆን የተገባ ነው ማለት ነው? እንግዲያውስ ፍቅር ከታገሰ፣ይቅር ካለ፣ካልታበየ….ለጥቅሜ ሳይሆን ለጥቅሟ አፈቅራታለው፡፡ ፍቅር ብቻ! ለገላዋ ሳይሆን ማንነቷን አፈቅረዋለው፡፡ ሠላሜን ለማግኘት በየሰአቱ ሰላሟን ላሳጣት አይገባኝም….ከጣፈጠው ማንነቴ ይልቅ ችኮነቴ እንዲታያት ማድረግ የለብኝም፡፡ ኖረችም አልኖረችም፤የሠው ሆነችም ብቸኝነቱ አማራት እሷ የልቤ ሰው ናት፡፡ በከፋ ቀኗ ቀና የምሆንላት፤ደስታዋን የምጋራላት ንፁህ ሴት፡፡ ሁሉም ኖርማል ሊሆን ይገባል…የእኔ እሷን እሷን ማለት እሷን ብቻ ሳይሆንም እኔንም አሰልችቶኛል…እርግጥ መፈቀሯን ሳትጠረጥር አልቀረም…ሴትነቷ ልቧን አሳልፋ እንዳትሰጥ አግቷት አፍቃሪዋን ችላ ለማለት ትሞክራለች፡፡ በቃ ወስኛለው ፍቅሬ የእውነት ነው…ማንነቷ ገዝቶኛል…
ከቀናት በፊት ስሞግተው ከነበረ አሳብ ያነቃኝ የጋሽ ሞላ ኮልታፋ አፍ ነበር፡፡ በባለከዘራው ጓደኛቸውና በቆንጆዋ የልጅ ልጃቸው ሚጡ ታጅበው አውራ ጎዳናውን አቋርጠው ተሻገሩ፡፡ አይኖቼ የሚጡ ደረት ኪስ ላይ ተሰክተዋል..በካቲካላ ናላቸው የዞረው ጋሽ ሞላ ከግራ ወደቀኝ እየተንገላቱ ሲያንገላቷት ከወደምስራቅ የፀሐይ ጨረር አርፎበት አይንን የሚያንከራትተው የሰማይን መስኮት የመሰለው ደረቷ አደብ ያስገዛል…ከጨባሹ ሽማግሌ አያቷ ይልቅ እሷ ላይ ማተኮሬ አቁነጠነጣት…አይን ለአይን ተጋጨን፡፡ ፈገግ አልኩላት…ጥርሶቿን ለይምሰል ከፈት አድርጋቸው እሩቅ ማየት ጀመረች፡፡ ምን አለ ባላየዋት….ይሄኔ በሽማግሌው የሳኩ መስሏት ማፈሯ ነው…ቲሽ…ይህን በማስብበት ቅፅበት አንገቴ ተከትሏት መጣመሙን አላስተዋልኩትም…ዞራ አየችኝ…ፀዳል ፊቷ ያበራል…ፈገግ አለች፡፡ ከንቱ ሽለላ፤ማየቴን ወደድኩት፡፡
     የሚጡን ፈገግታ እያሰብኩ መንገዴን ቀጠልኩ፡፡ ሁለት ወጣቶች አረግ ከወረሰው አጥር ስር ቆመው ይሟገታሉ፡፡ አጥሩን ተደግፎ የቆመው ወጣት እጁን ደረቱ ላይ አቆላልፎ አፉ የተቆለፈበትን ወጣት ያዳምጠዋል፡፡ ይጮኸል…ለማጣቱና ለመደኸየቱ የእናትና አባቱን ሞት ምክንያት አድርጎ ሞትን ይረግማል፡፡ ብቸኝነቱን መጠጡ ቅልጥፍናውን በነሳው ምላሱ እየተንዘባዘበ ይፈላሰፍበታል፡፡ አንጀቴን በላኝ…ቀረብ ብዬ ለማየት እርምጃዬን ገታ አደረኩት…ከሃያ አምስት እስከሰላሳ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚሆነው ወጣት ነው፡፡ ከንግግሩ ቤተሰቦቹ ከሞቱና የብቸኝነትን ሕይወት መግፋት ከጀመረ ዘመናት ያለፉ ይመስላል፡፡ ሁሌም ትላንት የሆነ ያህል የሚሰማው ነው የመሰለኝ….አንጀቴ ተላወሰብኝ…ሞትን አምኖ መቀበል አልቻለም ማለት ነው? ቀሪ ሕይወቱን በሙታን መንደር ሙት ሆኖ ሊኖር ፈርዶባታል፡፡ የቤተሰቡ ፍቅር የእግር እሳት ሆኖበት የቆመበትን እንዳያስተውል ጋርዶበታል ብዬ አስብኩ፡፡ ፍቅር ሁሉን አድራጊዋ…በጥሞና ያዳምጠው የነበረው ልጅ እጁን አፍታቶ ትከሻውን መታ መታ አድርጎ ምክሩን ያዥጎደጉደው ጀመር….መቼም ምክርና ቡጢ ለሰጭው ይቀላል፡፡ መካሪው ተሳክቶለት የተመካሪ ሕይወት ዳግመኛ ወደመሮጫው ትራክ እንዲገባ እየተመኘው ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡

     በመብራት ወደተንቆጠቆጠው ሱቅ አመራው፡፡ ሙዚቃው ቆሟል…ጆሮዬ በባለገመዱ ማዳመጫ ታፍኖ ኖሮ ሙቀቱ አልተለየኝም፡፡ የሞባይል ካርድ ለመግዛት ከሸቀጥ ሸማቹ ጋር ወረፋ ያዝኩ….አፍንጫዬ መልካም መአዛ ባለው ሽቶ ጥቃት ይሰነዘርበት ጀመር…ሽቶ ሰው እንደሚመርጥ በአንድ ወቅት ጓደኛዬ ያጫወተኝ ታውሶኝ የሽቶዋን ባለቤት ላይ ጓጓው፡፡ ዳሩ ጥላዬ ላይ ቆማ እንዴት ልዙር፡፡ ላስቀድማት ይገባኛል…ቦታዬን እየለቀኩ ወደ ጎን ተራመድኩ፡፡አሁን በግልፅ አያታለው….ሰረቅ አደረኳት….ቀልቧ ሸቀጡ ላይ ነው፡፡ ካርዱን ተቀብዬ መልሱን ስጠብቅ ባለሱቁ ከእሷ እንድቀበላት በአገጩ ጠቆመኝ፡፡ ጆሮዬ ላይ የጠለቁትን ባለገመድ ማዳመጫዎች መንቅሬ አውጥቼ እጄን ዘረጋውላት፡፡ የፊቷ ሙቀት ወላፈን ፊቴን አሞቀው….የተጠቀለለውን ባለ አስር ብር ኖት እንደተጠቀለለ እጄ ላይ አስቀመጠችው፡፡ ከብሩ ጋር የእጇ ሙቀት ሲጋባብኝ ይሰማኛል፡፡ ቀና ብላ አየችኝ…ሳቅ አለች…የፀደይ ወርን የመሰለው ፈገግታዋ ልቤን አሴት ሞላው፡፡ አንደበቴ እንደጠጣ ሰው ተቆላለፈብኝ….እጆቼን ዘርግቼ ደረቴን ገለጥኩት…ሁለቱንም እጆቿን በወገቤ አሳልፋ አቆላለፈቻቸው፡፡ ልጥፍ አለች፡፡ ማለዳዬ፣የልቤ ሰው፣ንግስቴ አይኖቿን ከድና የልቤን ምት ታዳምጣለች፡፡ ከአሳብ ባህር ሳልወጣ ወደቤን አገኘኋት፡፡ ዝም ያሰኘችኝ ዝምተኛዋ ደረቴ ላይ አንቀላፋች፡፡ ለካ ዝምታም ቋንቋ ነው….አትወደኝ ይሆን ብዬ ስባዝን የነበረችዋ ፀጥተኛዋ የንጋት ንፋስ ዝም ብላለች፡፡ ዝም ብቻ፡፡ የቃላትን ደካማነት በዝምታዋ አረጋገጠችልኝ፡፡ በዝምታ ውስጥ ያለ እረቂቅ ዓለም ፤እንደያሬድ ዜማ ልብን አሴት የሚያደርግ የፀጥታ ወጀብ…

1 comment:

  1. ግሩም ነው!! በቀጣዩ የተሻሌ ለአንባቢያን እንደምታቀርብ ተሰፋ አደርጋለሁ፡፡

    ReplyDelete