Friday, January 16, 2015

አንድ…ሶስት




አራት በአራት በሆነች ክፍል ውስጥ ረሃ እየሆኑ ነው፡፡ አንዱን ሲጥሉ አንዱን ሲያነሱ ታላቅ የአሳብ ባህር ውስጥ ገብተው ስለሕይወት ይፈላሰፉ ጀምረዋል፡፡ የፊት ገፅታቸው ተቀያይሯል….አይኖቻቸው ልውጣ ልውጣ የሚሉ ይመስላሉ፡፡ ፈጠዋል፡፡ የቤቱ ሙቀት የሲጋራው ጢስ ታክሎበት ፊትን ይጋራፋል፡፡ ሶስት ብቻ በመሆናቸው ተጠባብቆ ለማውራት አመችቷቸዋል፡፡የማህበረሰቡን ወግ መኮነን ተያይዘውታል፤ከግለሰብ ማንነታቸው ጋር ሊሄድ ባልቻለው ማህበረሰብ ውስጥ ተፈጥረው ማድረግ የፈለጉትን የሞራል ሕግ በሚል ጠፍሮ የያዛቸውን የቡድን ሕግ በማውገዝ ላይ ናቸው፡፡ ሞራል ደካሞችና ፈሪዎች ጠንካሮችን የሚያስሩበት ሰንሰለት መሆኑን መተማመን ችለዋል፡፡ The only good man is the man who succeeds የምትለዋ የኒቼ አሳብ አጥንታቸው ድረስ ዘልቆ ተሰምቷቸዋል፡፡ አሸናፊዎች ሁሌም ጉዞ ላይ ናቸው፤በጉዞው የደከሙትና መረሳት ያልፈለጉት የሞራልን ጉዳይ በማንሳት በጉዞዋቸው ርቀው እንዳይሔዱ ያደርጋሉ በዚህም በማህበረሰብ ውስጥ የሚበቅሉ አሸናፊዎች ነገራቸው ሁሉ ከማህበረሰቡ አመለካከት አንጻር እየተለካ ለውግዘትና ለመገለል ያበቃቸዋል፡፡
      ትምህርቷን ከአስራ ሁለተኛ ክፍል አቋርጣ ቤት ብትውልም መፅሐፍትን የማንበብ ክፉኛ መንፈስ ተጠናውቷታል፡፡ ማንንም ተናግሮ ማሳመን የተካነችው ለግላጋዋ ወጣት በሁለት ወንዶች መሃል ወሲብን ማውራት የቀለለ ተራ ነገር አድርጋዋለች፡፡ የሁለቱን ወጣቶች ጆሮ ለጉድ ተቆጣጥራዋለች፡፡ ታወራለች፤ይሰሟታል፡፡

Friday, January 9, 2015

ባህረ ሃሳብ

                   
አየሩ ለዐይን ይይዛል….በብርሃን ነፀብራቅ ውበታቸው የሚገዛን የቀኑ ሙሽሮች ጠቆርቆር ብለዋል፡፡ ለወትሮው በሚያማምር የብረት ዘንግ ተከበው በንፋሱ ግፊት ጣፋጭ በሆነው ለስላሳ ሙዚቃ የሚወዛወዙ አዲስ ሙሽሮች የሚመስሉት ዛፎች ውበታቸው ደብዝዞ ፀጥታ ውጧቸዋል፡፡በአርምሞ ላይ ይመስላሉ፡፡ በዚህ የፀጥታ ወጀብ በፀጥታ መንጎዱ አስፈራኝ፡፡ ይልቅ ከእጅ ስልኬ ላይ ዘፈን ከፍቼ መመሰጡን ምርጫዬ አደረኩት፡፡
     የኔ ፍቅር….ለካ እንዲህ እወድሻለው
     አብረን ሆነን መች አስቤው አውቃለው…….
ሙዚቃው ነው፡፡ እንደወትሮው የሙዚቃው መሳሪያ ቀድሞ ዘፋኙ ይከተላል ስል ዘፋኙ ቀድሞ መሪ ሆኖ አረፈው፡፡ የልጅ የመሰለ ቀጭን ድምፅ ሞቅ ብሎ ጆሮ ላይ ሲስረቀረቅ እንደ ጅብ ጥላ ከብዶ ሰብሰብ ብሎ የነበረው ደመና በሞቅታው ሲበታተን…የሞቀው አየር በአፍንጫዬ ቁልቁል ይተም ጀመር፡፡ ሞቅ አለኝ፡፡ ዙሪያዬን ከበው የሚያዜሙልኝ መላህክትን ያየው ያህል ደስ አለኝ፡፡
     ዳገቱን ጨርሼ አውራ ጎዳናውን ተቀላቀልኩት፡፡ ዘፋኙ መዝፈኑን ቀጥሏል፡፡
          እንዲህ ይጨንቃል ሆይ አንቺን መሸኘቴ
          ባዶ አረግሽኝ የእኔ አመቤቴ
          ሳይታሰብ በድንገት
ልክ ልኬን እየነገረኝ መሰለኝ….ደነገጥኩኝ…ከሳምንት በፊት ዘግቼው የነበረው አጀንዳ በእሊና የፍትህ ጓዳ ተቀሰቀሰ፡፡ ማን ይግባኝ ጠየቀ? ታሳሳኝ የነበረችው የጠዋቷ ፀሐይ የልቤን ንግስት ላላስጨንቃት ለራሴ ቃል ገብቼ ነበር፡፡

በልደቴ ቀን….


ዛሬ ኢየሱስ ተወልዷል፡፡ ልደቱን በሚገባ ላከብርለት እንደሚገባ እያንሰላሰልኩ ነው፡፡ ዛሬ ልዩ መሆን እንደሚገባኝም ይሰማኛል፡፡ የናርዶሱ ሽታ የናዝሪቱ ኢየሱስ…..የፍቅር አባት…..ዛሬ ምድርን እረገጣት፡፡ የምድር ላይ የመጀመሪያውን ሰከንዶች በለቅሶ ጀመረው፡፡ የሠላሙ አለቃ ሠላማችንን ሊሰጥ ለጥያቄያችን መልስ ይዞ በእናቱ እቅፍ ሆኖ እያለቀሰ ይህችን መራራ አለም ተቀላቀላት፡፡
     ጨቋኟ፣ቅብዝብዟ አለም አደቧን ልትገዛ ሰላሟን በበረት ተቀበለችው፡፡ ለሰላሟ ማረሻ የሚሆን ቦታ ጠፍቷት ስትባዝን ግርግም የነበረው ሠላሟ የከብቶችን ትንፋሽ ይሞቅ እንደነበር እንኳን ሳታስተውል ቀረች፡፡ ፍቅራችን ኢየሱስን ልታሞቀው በጨርቅ ጠቀለለችው…..የሠላም እናት የፍቅር መገኛ ንፁኋ ማሪያም፡፡ ደጉ ኢየሱስ አውን ምድር ላይ ነው፡፡ እንደሰው እንኖር ዘንድ፤ሰውን መሆን ሊያስተምረን ህፃኑ ግርግም ውስጥ ከከብቶች መሃል በጨርቅ ተጠቅልሎ ቅርጫት ውስጥ ተኝቷል፡፡ የአባቶች ምኞት፣የነቢያት ትንቢት፣የዳዊት የመዝሙሩ ቃና፣የስምኦን ናፍቆት መድሃኒት ዛሬ መጣልን፡፡
     ይህን በማውጠንጠን ላይ ሳለው የጓደኛዬ የእጅ ስልክ ያቃጭል ጀመር፡፡ አሳቤን ለሰከንዶች ገትቼ ዙሪያዬን እቃኝ ገባው፡፡ ሁሉም ውብ ነው፡፡ የሠላም ነፋስ፣የፍቅር ሙቀት፣የጠራ አየር….የአህዋፋት በረራ በራሱ ፍፁም ውበትን አይበት ጀመር፡፡ ከሩቅ የምሰማው የጉጉት ድምፅ ከዛፎቹ የአርምሞ እንቅስቃሴ ጋር ተደምሮ የማላውቀውን ዜማ ፈጥሮ ጭንቅላቴ ላይ ይጫወታል፡፡ ሙሉዋ ጨረቃ የዛሬውን ያህል አልደመቀችብኝም፡፡ ፀሐይዋን ለማሸነፍ ትግል ገጥማ የነበረችው ጨረቃ በሞት ሽረት ትግሉ የተሰነዘረባት የፀሐይ ጨረር ውበቷን ይበልጥ አፍክቷታል፡፡ እይታዬን የገታኝ ከፊት ለፊቴ የሚመጣው ሞርሳሳው ውሻ ነበር፡፡ ሞሪስ…የውሻው ስም ነው…አመጣጡ ለልፊያ እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ ልብሴን እንዳያበላሽብኝ ፈንጠር ብዬ አስቀድሜ ተነሳው፡፡ እንደወትሮው ጭራውን ወደላይ አኮፍሶ ያርገበግበዋል…ደስ ብሎታል፡፡ የሞሪስን የደስታውን ምንጭ ባላውቅም ቅብጥብጡን ውሻ አይቼ ቀኑን አሰብኩት፡፡ ሃስብ ወደነበረው ወደቀደመ ሃሳቤ ተመለስኩ፡፡